ዩኒቨርሲቲዎች እውነተኛ የመማሪያ፣ የማስተማሪያ እንዲሁም ጥናትና ምርምሮች የሚሰሩባቸው ትክክለኛ የእውቀት መፈለጊያ ሰላማዊ ቦታዎች ሊሆኑ ይገባል። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
————————————-
(የካቲት 27/2017 ዓ.ም) የትምህርት ሚኒስትሩ ኘሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በወለጋ ዩኒቨርስቲ በመገኘት ከዩኒቨርስቲው አመራሮችና ማህበረሰብ አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል ።
በዚሁ ወቅት ዩኒቨርሲቲዎች እውነተኛ የመማሪያ፣ የማስተማሪያ እንዲሁም ጥናትና ምርምሮች የሚሰሩባቸው ትክክለኛ የእውቀት መፈለጊያ ሰላማዊ ቦታዎች ሊሆኑ ይገባል፤ ለዚህም በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ እየተተገበሩ ያሉ የሪፎሮም ሥራዎች አላማ ይህን ለማሳካት መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም የዩኒቨርሲቲዎችን አስተዳደር፣ አስተሳሰብና አጠቃላይ ባህል መቀየር አስፈላጊ በመሆኑ የዩኒቨርቲውን አመራር የመቀየር ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች የአካባቢያቸውን ፀጋ በመለየት ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ የህብረተሰቡን ህይወት መቀየር እና ለሀገራቸው ችግር መፍትሔ መፈለግ ይገባቸዋል ያሉ ሲሆን በዚህ ረገድ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የአስተዳደራዊ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሰለሞን አብርሃ (ዶ/ር) በዩኒቨርሲቲው በተደረገ ሱፐርቪዥን በጥንካሬና መሻሻል ያለባቸውን ተብለው የተለዩ ጉዳዮችን ለውይይት መነሻ አቅርበዋል።
በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት አዲስ የተመደበው አመራር የተጀመሩ ሥራዎችን በሚገባ በመፈተሽ የትምህርት ጥራትን የሚያረጋግጡ ጉዳዮችን ቅድሚያ በመስጠት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ተስፋዬ ለማ (ዶ/ር) በበኩላቸው የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች በዩኒቨርሲቲው መገኘት ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግና ተጠያቂነትን ለማስፈን ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፀው ዪኒቨርሲቲው የአመራር ለውጥ ከተደረገለት በኋላ የትምህርት ጥራት ፕሮግራሞች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
አክለውም ዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን ተልዕኮ በሚገባው መጠንና ጥራት ለማሳደግ አስተሳሰባችንና አሰራራችንን በማሻሻል ያለንን አቅም አሟጠን መጠቀም ይጠበቅብናልም ብለዋል።
አመራሮቹ በነቀምቴ ከተማ በነበራቸው ቆይታ የዩኒቨርሲቲውን ኮምፕሬንሲቭ ሆስፒታል ጨምሮ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።



