ጥር 25/2016 ዓ.ም (ትምህርት ሚኒስቴር) የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ የ2016 በጀት አመት ዕቅድ አፈፃጸምን አስመልክቶ ምክክር ከክልልና ከተማ አስተዳደሮች ትምህርት ቢሮዎች ጋር አካሂዷል ::

በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ አየለች እሸቴ፤ የትምህርት ጥራት ችግሮችን ለመቅረፍና የትምህርት ተደራሽነትን፣ ተሳትፎንና ፍትሃዊነትን ለማሳደግ የተለያዩ የለውጥ መርሃ- ግብሮች ተቀይሰው ወደ ትግበራ መገባቱን ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ እንደገለጹት የአጠቃላይ ትምህርት ስርዓተ ትምህርት ትግበራ፣ የመማሪያ መጻህፍት ህትመትና ስርጭት እንዲሁም የመምህራንና ትምህርት አመራሮች አቅም ግንባታ ችግሮቹን ለመቅረፍ እየተሰራ ሲሆን ቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል::

ክብርት ወ/ሮ አየለች አክለውም የጀመርናቸውን የለውጥ መርሃ-ግብሮች ውጤታማ ማድረግ የሚቻለው ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንዲያደርጉና የድርሻቸውን እንዲወጡ ማስተባበር ስንችል ነው ብለዋል::

በምክክር መድረኩ በበጀት ዓመቱ የ6 ወራት ዕቀድ አፈጻጸም ሪፖርት ሁሉም የክልልና ከተማ አስተዳደሮች አቅርበዋል። በአተገባበር ወቅት የነበሩ መልካም ተሞክሮዎች ተጠናክረው ስለሚቀጥሉበትና በአፈጻጸም ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዲቀረፉ የመፍትሔ አማራጮች ተመላክተዋል፡፡

በማጠቃለያው በኦሮሚያ ክልል የአዳማ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተሞክሮ ሁሉም ተሳታፊ በትምህርት ቤቱ ተገኝቶ እንዲጎበኙና ልምድ እንዲያገኙ ተደርጓል።

በመድረኩ ላይ የክልል የትምህርት ቢሮ ሃላፊዎች የመምህራን ማህበር ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ አመራሮች ተሳትፈዋል።