ጥር 26/2016 ዓ.ም (ትምህርት ሚኒስቴር) በአደዛዥ እጽና መድሃኒቶች ሥርጭት ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የአስተዳደር ጉዳዮች ዴስክ ኃላፊ አቶ አብዶ ናስር በዩኒቨርሲቲዎች የአደንዛዥ እጽና መድሃኒቶች ተጠቃሚነት ችግሮችን ለመከላከል ሥራዎች ሲሰሩ የቆዩ ቢሆኑም ከችግሩ ስፋትና ባህሪ አንጻር የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡

አቶ አብዶ ናስር አክለውም ችግሩን ለመፍታትም አደንዛዥ እጾችና መድሃኒቶች ወደ ተቋማቱ እንዳይገቡ ከባለድርሻ አካላት ጋር የቁጥጥር ስራዎችን ከመስራት ጎን ለጎን በጉዳዩ አሳሳቢነት ዙሪያ መንስኤዎችን፣ልምዶችንና መፍትሄዎችን መሠረት ያደረጉ የባህሪ ለውጥ ሊያመጡ በሚችሉ የተማሪ ሥልጠናዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጤንነቱ የተጠበቀ ትውልድ ለመቅረፅ ፤ ስብዕናን በመገንባትና ግንዛቤ በመፍጠር የባህሪ ለውጥ ለማምጣት በትኩረት መሰረት እንደሚገባም ገልጸዋል።

ሀላፊው አክለውም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት በችግሩ አሳሳቢነት ልክ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅንጅትና በትኩረት ሊሠሩ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለሥልጣን የነርኮቲክና ሳይኮትሮፒክ መድሃኒቶች እና ትምባሆ ቁጥጥር ባለሙያ ወ/ሮ ብጽዓት ሸመልስ በበኩላቸው አደንዛዥ እጽና መድሃኒቶች የአዕምሮ ጤናን በመጉዳት ዜጎችን ከአላማቸው በማደናቀፍ ህይወታቸውን የሚያበለሹ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ እነዚህን አደንዛዥ እጾችና መድሃኒቶችን በአይነታቸው፣ምንነታቸውና በሰዎች አእምሮ ላይ በሚያደርሱትን የጉዳት ደረጃ ተረድቶ እንዳይመረቱ፣እንዳይሰራጩና ጥቅም ላይ እንዳይውሉ በመከላከል የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ወ/ሮ ብጽዓት ጠቁመዋል፡፡

የመቋሚያ የማህበራዊ ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤሊያስ ካለአዩ በበኩላቸው አደንዛዥ እጾችና መድሃኒቶችን በመከላከል ለምንወዳትና ለምንሳሳላት ሀገራችን የአዕምሯቸው ጤና የተጠበቀ ትውልድ ልናበረክት ይገባል ብለዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተለያዩ ጽሑፎች ቀረበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ከትምህርት ሚኒስቴር፣ከጤና ሚኒስቴር፣ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለሥልጣን እና ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡