በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዲጂታል ትምህርትን ለማስጀመር የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሲከታተሉ የነበሩ መምህራን ተመረቁ::

ታህሳስ 06/2016 ዓ.ም (ትምህርት ሚኒስቴር) በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዲጂታል ትምህርትን ለማስጀመር የአቅም ግንባታ ሥልጠና በአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሲከታተሉ የነበሩ መምህራን አጋሮችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ማክሰኞ ታህሳስ 2 ቀን 2016 ዓ/ም በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀዋል።

ከተለያዩ የኢትዮጵያ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ 32 መምህራን ለ8 ወራት በአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሜሪ ሉ ፉልተን መምህራን ኮሌጅ በInstructional Design and Performance Improvement ስልጠናቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ሲሆን በዕለቱ በግራጁዌት ሰርተፊኬት ተመርቀዋል፡፡

በተጨማሪም በዕለቱ የዲጂታል ትምህርት አዘገጃጀት የአሰልጣኞች ስልጠናን በኮሌጁ ሲከታተሉ የቆዩ 19 መምህራንም ተመርቀዋል፡፡

በምርቃ መርሃግብሩ የተገኙት የትምህርት ሚኒስቴር የአካዴሚክ ጉዳዮች ዋና ስራ አሰፈፃሚ ዶ/ር ዔባ ሚጀና፣ የe-SHE ፕሮግራም የሚያካሄደው የመምህራን አቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ለሚኒስቴሩ የሰው ሃብት ልማት ስትራቴጂ ያላቸውን አበርክቶ አፅንዖት በመስጠት የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

ተመራቂ መምህራኑም የትምህርት ሥርዓቱን ለማዘመን በመማር ማስተማር ስልቶች፣ በትምህርት ካሪኩልሙና ፔዳጎጂው ላይ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ረገድ ከፍተኛ አበርክቶ እንደሚጠበቅባቸው አሳሰበዋል፡፡

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአይሲቲና ዲጂታል ትምህርት መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ዘላለም አሰፋ በበኩላቸው መንግስት ባለፉት ዓመታት የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ መስራቱን አስታውሰው በመጪዎቹ 10 ዓመታት ዩኒቨርሲቲዎችን ከማስፋት ይልቅ የትምህርት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማሻሻል እንደሚሰራና ለዚህም ስኬት አንዱና ዋነኛ አማራጭ የዲጂታል ትምህርት እንደሚሆን ጠቁመዋል።

የማስተርካርድ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶ/ር ሳሙኤል ያለው በበኩላቸው ኢ-ለርኒግ የዘመኑን ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የትምህርት ሥርዓቱን ጥራት፣ ፍትሃዊነትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥና ወጣት ተማሪዎችን ለሥራ ዓለምና ለሥራ ፈጠራ የበቁ እንዲሆኑ ለማስቻል ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዑባ አደም ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማሩን ሂደት በቴክኖሎጂ የተደገፈና የተሳለጠ ለማድረግ ከፍተኛ አእንቅስቃሴ ሲያድርግ መቆየቱን ጠቅሰው በምስራቁ የኃገሪቱ ክፍል ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች በፕሮግራሙ Resource Center ተብለው ከተለዩ አምስት ዩኒቨርስቲዎች መካከል እንዲካተት ያስቻልው እነዚህ የአይሲቲ የመሰረተ ልማት ስራዎቸ እንድሆኑ እናምናልን ብልዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን፣ ከአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ፣ ከሻያሾኔ እና ከ50ዎቹ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን እየተገበረ ያለው የአምስት ዓመት ፕሮጄክት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዲጂታል ትምህርትን ተቋማዊ ለማድረግና ለማጎልበት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆኝ ለመምህራንና ተማሪዎች ጥራታቸውን የጠበቁ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን መስጠት ከዋናዎቹ ተግባራት ውሰጥ ግንባር ቀደሙ ነው፡፡

በዚህም አሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ ከፕሮጄክቱ ጋር በመሰረተው አጋርነት እስከ አሁን Master Class Training፣ Master Class Training of Trainers እና Instructional Design and Performance Improvement የተሰኙ የመምህራን የዲጂታል ትምህርትን የመቅረጽና የማዘጋጅት አቅምን የሚገነቡ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ የቆየ ሲሆን በአቅም ግንባታ የትኩረት አቅጣጫው የመምህራንና የተማሪዎችን የዲጂታል ትምህርትን የመስጠትና የመከታተል አቅምን የመገንባት እቅድን ይዞ 35,000 መምህራንንና 800,000 ተማሪዎችን ለመድረስ እየሰራ ይገኛል።