ታህሳስ 13/2016 ዓ/ም (ትምህርት ሚኒስቴር) የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንቶች ፎረም ተጠናቀቀ።

በትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና ማህበረሰብ ጉድኝት ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሰለሞን ቢኖር  በፎረሙ ማጠቃለያ ምርምር ለሀገር እድገትና ልማት ያላቸውን አስተዋጾ  ጠቅሰው ፎረሙ ሀገራዊ የምርምር ስራ ማነቆዎችን በመለየት በሳይንሳዊ መንገድ ግንዛቤ መፍጠር ይጠበቅበታል ብለዋል።

ዶ/ ሰለሞን ምርምሮች  ሀገራዊ የትኩረት መስኮችን  ያማከሉና  ችግር ፈቺ ሊሆኑ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ከአፈጻጸም አንጻርም የከፍተኛ ትምህርት ፣ ቴክኒክና ሞያ ሥልጠና፣ ምርምር ተቋማትና ኢንዱሰትሪ ትስስር አዋጅ 1298/2015 ጋር እያጣጣሙ መተግበር እንደሚገባ አመላክተዋል።

የማህበረሰብ ጉድኝት ስራዎች  እውቀት መር መሆን እንዳለበት የጠቀሱት መሪ ስራ አስፈጻሚው  መምህራን በእውቀታቸው ማህበረሰቡን በሚያገለግሉበትና  ማህበረሰቡ ጋ ያሉ ሀገር በቀል እውቀቶችንም በሚጠቀሙበት አግባብ ሊመራ እንደሚገባው ገልጸዋል።

ዩኒቨርሰቲዎች በኢትዮጵያ ብቻ በሚገኙ ብዝሐ-ህይዎት ላይ ከአለም ዓቀፍ ድርጅቶች ጋር ምርምር በሚከናወኑበት ጊዜ የምርት ባለቤትነት ጥቅም እና የናሙና ዝውውር  መርሆዎቾ ጋር በተናበበ አግባብ በጥንቃቄ ሊመራ እንደሚገባው አስታውሰዋል።

በፎረሙ የከፍተኛ ትምህርት ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ምርምር ተቋማት እና ኢንዱስትሪ ትስስር አዋጅ ቁጥር 1298/2015 በአቶ ተሾመ ዳንኤል የተቋማት ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዴስክ ሀላፊ ፣ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ምርምር አስተዳደር እና ማህበረሰብ ጉድኝት ረቂቅ መምሪያዎች በዶ/ር  ተስፋማርያም  ሽመክት ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

በተጨማሪም  ሀገራዊ የምርምር ስነ-ምግባር አሰራር ስርዓት እንዲሁም የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ተግባራት  አፈጻጸምም ቀርበው የተሞክሮ ሽግግር ተደርጓል  ።

በፎረሙ ማጠቃለያ የመንግሥትና ግል ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንቶች፣  እና የትምህርት ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ባለሙያዎች የቦንጋ ዩኒቨርስቲ ምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ላይ የመስክ ጉብኝት አድርገዋል።