“የትምህርት ስብራቱን ለማከም ከታች ጀምሮ በየደረጃው መሠራት ያለባቸው ብዙ የቤት ስራዎች አሉብን ” ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ

የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ብሄራዊ ፈተና ውጤትን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጠ


መስከረም 28/2016 ዓ.ም (የትምህርት ሚኒስቴር)የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ብሄራዊ ፈተና ውጤት አስመልክቶ  በትምህርት ሚኒስቴር መግለጫ ተሰጥቷል።

ተማሪዎች ውጤታቸውን ከነገ ጠዋት መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ  በድረ-ገጽ እና በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ማወቅ እንደሚችሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ሮ ብርሀኑ ነጋ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሠጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።

ሚኒስትሩ  እንደተናገሩት በ2015 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ብሄራዊ ፈተና  ከወሰዱ 845 ሺህ 188 ተማሪዎች ውስጥ 27 ሺህ ተማሪዎች ከ50 በመቶ በላይ በማምጣት የማለፍያ ውጤት ማስመዝገባቸውን ገልፀዋል።

ፈተናውን ከወሰዱት ውስጥ 3.2% ተማሪዎች ብቻ ማለፋቸውን የገለፁት ሚኒሰትሩ ውጤቱ  ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር በ0.01 መቀነሱንም አብራርተዋል።

ዘንድሮ 3 ሺህ 106 ትምህርት ቤቶች ፈተና ያስፈተኑ ሲሆን፣ ከነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1 ሺህ 328 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ ማሳለፍ አለመቻለቸውን መታየት ያለበት ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም 42.8 ከመቶ ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ አለማሳለፋቸው ነው የተገለፀው።

የዘንድሮው  ትልቁ የፈተና ውጤት 649 ሲሆን ይኸውም በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት መስክ በሴት ተማሪ የተመዘገበ ሲሆን በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 533 ከ600  ከፍተኛ ውጤት ሆኖ በወንድ ተማሪ  የተመዘገበ መሆኑ ተገልጿል።